በአብዱረዛቅ መሐመድ
በእስልምና
ታሪክ የመጀመሪያው አዛን አድራጊ (ሙዓዚን) ቢላል ኢብን ረባህ (رَبَاح ٱبْن بِلَال) የተወለደው ነብዩ
መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ከተወለዱበት መካ (ቅዱስ ከተማ) ውስጥ ሲሆን ታማኝና በነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ልብ ዉስጥ
ልዩ ቦታ የነበረው ሰሐባ ነበር። ቢላል እስልምናን የተቀበለዉ በወጣትነት እድሜው ነበር።
በጣም ውብና
ልዩ በሆነው ድምጹ የሚታወቀው ቢላል ከእስልምና በፊት በነበረው ህይወቱ “ባሪያ” ነበር። ወላጆቹም ከሐበሻ ምድር
(ኢትዮጵያ) ወደ መካ የሄዱ ባርያዎች ስለመሆናቸው በታሪክ ተጽፎ ይገኛል። የቢላል አባት ረባህ ሲሆን እናቱ ደግሞ
ሐማም ትባላለች። እንዲሁም ባለቤት ደግሞ ሂንድ ትባላለች።
ቢላል አል ሐበሽይ፣ ቢላል ኢብን ሪያህ እና ቢላል ኢብን ረባህ ይጠራባቸው ከነበሩ ሶስት ስሞች ናቸው።
ቢላል
ከእስልምና በፊት በነበረው ህይወቱ የበኒ ጁመሃ ጎሳ አባል የነበረው የኡመያ ኢብን ኸለፍ ባሪያ ነበር። አንድ ቀን
ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በነብይነት የመላካቸው ዜና የመካ ህዝብ ሲቀባበለው ከቢላል ጆሮ ደረሰ። የቢላል አሳዳሪ
ከእንግዶቹ ጋር ስለ ነብዩ መላክ እና ጣዖታቸውን እንደሚቃወም በንዴት እየተብሰለሰለ እና ሴራ እያውጠነጠነ ሲናገር
ቢላል ሰማ፤ ቢላል ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ስለተነሱበት ዓላማና ስለሚያስተምሩት ትምህርት ግንዛቤ ሊያገኝ ቻለ።
አዲስ የመጣው ሐይማኖት ለአካባቢው ማህበረሰብ እንግዳ ነገር እንደሆነና እና ስር-ነቀል ለውጥ
ለማምጣት ያለመ ስለመሆኑ፤ ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ምንም እንኳን “ነብይ ነኝ” ብለው በመናገራቸው ተቃውሞ
የገጠማቸው ቢሆንም ታማኝ፣ እውነተኛ እና በስነ ምግባር የታነጹ ስለመሆናቸው ቢላል ከነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ)
ጠላቶች አንደበት አደመጠ። “መሐመድ አንድም ቀን ዋሽቶ አያውቅም፤ ጠንቋይም ሆነ እብድ አይደለም:... ሆኖም ዛሬ
እኛ እርሱን በነዚህ ነገሮች መጥላት ይኖርብናል። ወደ እርሱ የሚጎርፉትን ሰዎች መግታት የምንችለው በዚህ መንገድ
ነው።” በማለት ሲዶልቱ ቢላል ታዝቧል።
ከእለታት በአንዱ ቢላል የእምነት ምርጫውን ይፋ ማድረግ
እንዳለበት ወሰነ፤ ወደነብዩ መሐመድ በመሄድ እስልምና ለመቀበል መወሰኑን ይፋ አደረገ። በዚህን ጊዜ የቢላል መስለም
በመካ ምድር ተሰራጨ። የበኒ ጁመሃ መሪዎች ይህን ዜና ሲሰሙ ክፉኛ ተቆጡ፤ በተለይም ኡመያ ኢብን ኸለፍ የተባለው
የቢላል አሳዳሪ የ”ባሪያ”ው መስለም እንደ ታላቅ ነውር እና ንቀት ቆጠረው። ኡመያ እንዲህም አለ፥ “ይህ ኮብላይ
ባሪያ በመስለሙ ጸሀይ ተመልሳ የምትጠልቅ አይመስለኝም”
ኡመያና የበኒ ጁመሃ ጎሳ መሪዎች ለቢላል
ከእስልምና እንዲወጣ እና በወቅቱ ይመለኩ በነበሩት ”ላት እና ኡዛ” በሚባሉ ጣዖታት እንዲያምን ደጋግመው ጠየቁት።
ቢላል ግን እስልምናውን አጥብቆ እንደሚይዝ ገለጸለት። ሊያምንላቸው ስላልቻለ በመካ በረሃ በጸሀይ በተቃጠለ አሽዋማ
መሬት ላይ አስሮ አስተኝተውና ሆዱ ላይ ትልቅ ድንጋይ አስቀምጠው በግርፋት ሲቀጡት ቢላል ግን ከስጋዊ ህመም
መንፈሳዊ የበላይነትን በመምረጡ ለጠላቶቹ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም። ይልቁንም በተደጋጋሚ “አሐድ!
አሐድ” አሐድ! ... “ በማለት የአምላክን አንድነት ያውጅ ነበር።
ቢላል በርካታ ኢሰብዓዊ ድርጊት
ተፈጽሞበታል። የበኒ ጁመሃ ጎሳ መሪዎች አንድን ባሪያ አሳምነው ወደ ቀድሞ እምነቱ ሊመልሱት ባለመቻላቸው ቁጭት እና
ሀፍረት ተሰማቸው፤ ክብራቸውን ለመጠበቅ ሲሉ ቢላል ቢያንስ ስለ አማልክቶቻቸው ጥቂት በጎ ነገር እንዲናገር
ቢጠይቁትም አሻፈረኝ አለ። ህይወቱን ከስቃይ ምናልባትም ከሞት ለማዳን ከልቡ ባይሆንም እንኳ ቢያንስ ስለ
አማልክቶቻቸው ጥሩ መናገር በቂው ነበር። ቢላል ግን ለኢስላም ብቻ ሳይሆን ለመላው የሰው ዘር የሚያኮራ ጠንካራ
አቋም ወሰደ።
“እኛ የምንለውን ደግመህ በል” በማለት ይገርፉታል። እሱም “እናንተ የምትሉትን ለመናገር
ምላሴ አይችልም” ይላቸዋል። በዚህን ጊዜ ነበር አቡበክር ሲዲቅ (ረ.ዐ.) የመጡት። አቡበክር መጡና ቢላልን ከኡመያ
ለመግዛት ተስማሙ። አቡበክርም ቢላልን ለራሳቸው ባሪያ ሊያደርጓቸው አልፈለጉም፤ ይልቅ ከስቃዩ ገላግለው ነጻነቱን
አወጁለት።
ነጻነቱን ካገኘ በኋላ ወደ ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በመሄድ ሙሉ ጊዜውን ለእስልምና ሰጠ።
ነብዩ መሐመድም ቢላልን ለአዛን አድራጊነት (ሙዓዚንነት) መረጡት። በተጨማሪም የመዲና የግምጃ ቤት (በይተል ማል)
ኃላፊ አድርገው ሾሙት። ቢላል በዚህ የግምጃ ቤት ኃላፊነት እያለ ባላቸው ለሞተባቸው ሴቶች፣ ለወላጅ አልባ
ህጻናት፣ ለመንገደኞች እንዲሁም እራሳቸውን መርዳት ለማይችሉ ሌሎች ሰዎችም የገንዘብና ቁሳቁስ አከፋፍሏል።
ሙሐመድ
አብድልረዑፍ የተባለ ጸሐፊ ስለ ቢላል በጻፈው መጽሃፉ፥ “ቢላል ውብና ማራኪ የሰውነት ቅርጽ፣ ጥቁር ቡናማ የፊት
ቀለም፣ አብረቅራቂ አይኖች፤ የተስተካከለ አፍንጫና የጠራ ቆዳ ነበረው። በተጨማሪም ወፍራም፣ ሙዚቃዊ ቃና ያለውና
አስገምጋሚ ድምጽ የታደለ ሰው ነበር። እንዲሁም በሁለቱም ጉንጮቹ በኩል ሳሳ ያለ ጺም ነበረው። ቢላል ትልቅ እውቀት
የተቸረው፣ ለራሱ ክብር የሚሰጥና በራሱ የሚተማመን ሰው ነበር” ይላል።
ዊልያም ሙዒር የተባለ ጸሃፊ
በበኩሉ፥ “ቢላል ረጅምና ጥቁር ሲሆን አፍሪካዊ የፊት ቅርጽና ጥቅጥቅ ብሎ የሚበቅል ጸጉር ነበረው።” ጸሐፊው
አክሎም የቁረይሽ ጎሳ አባላት ቢላልን ‘የጥቁር ሴት ልጅ’ (“ኢብን ሰውዳ/Ibn Sawda”) እያሉ ይሰድቡት
ነበር” ብሏል።
ቢላል ኢብኑ ረባህ ጓደኞቹ ሲያሞጋግሱት አንገቱን ይደፋ እንደነበርና አይኖቹን በትዝታ
ገርበብ አድርጎ “ትናንት ባሪያ የነበርኩ ሀበሻ ነኝ” ይል ነበር። እነሱ ግን “የእኛ ልዑል” ብለው ይጠሩት
እንደነበር ታሪክ ጽፏል።
ቢላል የተወለደው በፈረንጆቹ መጋቢት 05፣ 580 ሲሆን ህይወቱ ያለፈው ግን ከ638-40 ባለው ጊዜ ውስጥ (ከዚህ ጋር በተያያዘ ያሉ መረጃዎች የተለያዩ ናቸው) እንደሆነ ይነገራል።
ምንጮች፦
Study papers and documents titled:
Bilal ibn Rabah
The Life of Muhammad
Lessons from the Lives of the Sahaba
Bilal ibn Rabah: The symbol of human equality