Wednesday 29 April 2020

ኢማም ሐሰን ኢንጃሞ


በአብዱረዛቅ መሐመድ


ሐሰን ኢንጃሞ ምን ያህል እናውቃቸዋለን? ከጀግንነታቸው በተጨማሪ ሲበዛ ሐይማኖተኛ እና ሰብዓዊነት የተላበሱ እንደነበሩስ እናውቃለን?
ሼህ ዑመር ሼህ በሽር (ከ1860-1923 ዓ.ም) በአረብኛ በጻፉትና ሼህ አብደላህ መሐመድ አሊ “ጥሮነ - የኢትዮጵያ ቀደምትና ታላላቅ ዑለማዎች ታሪክ” በሚል ርዕስ ወደ አማርኛ በተረጎሙት መጽሃፍ እንደተገለጸው፥ ሐሰን ኢንጃሞ ከቁመቱ ረዘም ብሎ ቀጠን ያለ፤ ብዙ የማይበላና የማይጠጣ፤ ጥቁር ቢሆንም ቆንጆ ፊት ያለው፤ ጀግናና በዚህ ሙያውም ማንም የማይደርስበት፤ ከጀግኖች ሁሉ ፈረሰኛ የሆነ፤ ከፈረሰኞች ሁሉ ጀግና የነበረ፣ ከፈረሱ ላይ ወርዶ መጋደልን የሚወድ፤ የትም ቢሆን በጀግንነቱ የሚታወቅ፤ ለጦርነት በሄደበት ሁሉ ድልም ተከትላው የምትሄድ፤ ብቻውን ሆኖ እንደ ብዙ የሚቆጠር ስመጥር ጀግና ነበር።
ኢማም ሐሰን ኢንጃሞ በዲኑ ላይ ለስደት የተዳረገ፤ ብዙዎችንም ያስከተለ፤ ሸሪዓ ድል እንዲያደርግ ያስቻለ፤ በበጎ ሕይወት የተሞላ፤ ጥመትን ያስወገደ፤ ኢማምነትን ያወጀና በሰሃባዎች መንገድ የተጓዘ . . . ታላቅ መሪ ሆኖ አልፏል።
ጦርነት በተጋጋመበት ወቅት ከ’ርሱ ወገን የሆነ አጋዥ ያለ የማይመስለው፤ ጠላቶቹን ብቻውን እያጨደ ለመጨረስ ሳንባው የሚከፈት፤ አጋዦቹ ካሉም ከ’ርሱ ጀርባ ሆነው የሚጠለሉበትና ጋሻቸው የሆነ፤ ይህንንና መሰል ባህሪዎችን ተላብሶ ጠላቶቹ ሲመለከቱት ያለ ጦርነት የሚሸነፉለት፤ እርሱና ከ’ርሱ ጋር ያሉት ደግሞ በአሸናፊነት ምርኮዎችን እያፈሱ እንዲመለሱ የሚያደርግ ወደር የሌለው ጀግና ነበር።
ይህም ገጽታውና ባህሪው ከ’ርሱ ጋር የቆየ ሲሆን ከስደቱ በፊት፣ በስደቱ ጊዜና ከስደቱ በኋላም ጠላቶቻቸው የ’ርሱን ድምጽ ከሰሙ ለመጋደልና ከፊቱ ለመቆም ቀርቶ እግራቸው ርዶ ይፈረጥጡ ነበር። አብረውት የሚዘምቱ ሰዎች ምርኮዎችን ለመሰብሰብ በሚራወጡበት ወቅት እንኳ እርሱ ትኩረቱ ለሱ ሳያደርግ የጠላት ፈረሰኞችን በዓይነ-ቁራኛው የሚጠብቅና ካገኛቸውም ብቻውን ገጥሞ የሚጥላቸው፤ የጀግኖች ጀግና እንደነበር በሁሉም ዘንድ ተመስክሮለታል።
ሐሰን ኢንጃሞ ሲበዛ ቸር እንደነበር ይገለጻል። ለዚህ ምሳሌ እንዲሆን አንድ ታሪክ እናንሳ። የቀቤና ሰዎች በከብት ብዛት የታወቁ ቢሆኑም እርሱ ግን ለዚህ አልታደለም ነበር። ምክንያቱም እርሱ ዘንድ የሚመጡ ከብቶች ለሚስኪኖችና ለወታደሮች ስንቅነት ከመታረድ አልያም ለዘማቾች ከመታደል አይድኑምና ነው።
በአንድ ወቅት ከቀቤና ህዝቦች ጋር ዘምቶ በተመለሰበት ጊዜ ለቤተሰቦቹና ለራሱ እንዲያደርጋቸው ተብሎ 30 ከብቶች ተሰጥቶት ነበር። ሼህ ዑመር (ከላይ የጠቀስኩት መጽሃፍ ጸሃፊ) እነዚህን ከብቶች ለማንም እንዳይሰጥ ወይም እንዳያርድ አስምለዉት ነበር። ነገር ግን አስራ አምስት ቀናት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሁሉም ጨርሷቸው ተገኘ።
በአጠቃላይ ሐሰን ኢንጃሞ ለሸሪዓው ተገዢ የሆነ፣ ቁርዓንን በብዛት መቅራት የሚወድ፣ ከዑለማዎች ጋርም በመቀመጥ ብዙ የሚሰማ ነበር። ሐሰን ኢንጃሞ ማለት ግርማ ሞገስ ያለውና በአጋጣሚ ካልሆነ በቀር የማይስቅ፤ ትጥቁን አንድም ቀን ያልፈታና መሳሪያውን ከራሱ የማይለይ፤ በመስጂድ የሰዎች ጥሪ አድራጊ (ሙዓዚን) እና አገልጋይ የሆነ ነበር።
ሐሰን ኢንጃሞ ከልግስናው የተነሳ አባጅፋር ሰጥተዉት ከነበረው ብዙ ብር 4 ሪያል ብቻ ይዞ ተገኘ። የተረፉትንም ሁለቱን ለሼህ ሱለይማን፤ አንዱን ለሼህ ሁሴንና ቀሪ አንዱን ደግሞ ለሼህ አብድሽኩር ሰጥቶ ተገላገለ። አባቱም እንደዚሁ በጀግንነት፣ በፍትሃዊነት፣ በቃል አክባሪነት፣ ድሆችንና ወላጅ አልባዎችን በመርዳት የታወቁ ነበሩ።
ሐሰን ኢንጃሞ ወደ ጅማ ሄዶ ሲመለስ ቃቄ በምትባል ቦታ ላይ ወባ መሰል ህመም ነክቶት ክፉኛ ታመመ፤ ቤቱም ደርሶ አረፈ።

Tuesday 28 April 2020

ሐበሻን (ኢትዮጵያን) ከሌሎች ሙስሊም ሀገራት ልዩ ከሚያደርጓት ነገሮች በጥቂቱ





በአብዱረዛቅ መሐመድ



=> ነብዩ መሐመድን (ሰ.ዐ.ወ.) ያጠባን በመሆናችን፦ በረካ (ዑሙ አይመን በረከተል ሐበሻ) የተባለች ሴት የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ.) እናት በሞቱ ጊዜ ነብዩን ተንከባክባና ጡቷን አጥብታ ወደ አያታቸው አብዱልሙጠሊብ ዘንድ ያደረሰች ሐበሻዊት ናት። በዚህም የማጥባት ሂደት ከነብዩ ዘር ጋር በመቀላቀሏ ሐበሾች የሆኑት አባቷ፣ ወንድሟ፣ እህቷ . . . . የዘር ሀረጓ ሁሉ ከ’ርሳቸው ጋር በመቀላቀሉ ክብሩ ይደርሳቸዋል። (የጋራ ጡት የጠቡ ማናቸውም ልጆች በሸሪዓ ወንድማማቾች/እህትማማቾች ናቸው)
እንዲሁም ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ.) ለበረካ ክብር ሲሉ ጋቢያቸውን መሬት አንጥፈው እንድትቀመጥበት ማድረጋቸው አይዘነጋም። ይህም ከእርሷ ጋር የመጡትን ሁሉ ክብር ያጎናጸፈ ነበር። (ነብዩ መሐመድ በህይወት በነበሩበት ጊዜ በረካ የጀነት መሆናቸው መስክረውላቸዋል ይባላል)።
ቡሰይሪ የተባሉ ዓሊም “ሀምዚያ” በተባለው የግጥም ስራቸው ላይ እንዳስቀመጡት ዑሙ አይመን ለነብዩ አጥቢያቸው እንደሆነች ገልጾ ክብሯ “የሰማይ ያህል የሰፋ ነው” ብለው ገልጸዋቸዋል። በመቀጠልም ይህ አሊም የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ.) ጋቢ ጉዳይ ጠቅሰው የሐበሻን ታላቅነት፣ ጀግንነትና የጦር ኃያልነት በዚያ ጊዜ ሳይቀር የታወቀና ነገራቸው ሁሉ ጠንቃቃነት የተሞላበት እንደሆነ አሳውቀዋል።
=> አረቦች እንዳይተናኮሉን ነብዩ ማዘዛቸው፦ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ.) “ሐበሾችን ሳይነኳችሁ አትንኳቸው” ብለዋል።
=> የሀበሻ ሰዎች ጥሩነት በቁርዓን ውስጥ መገለጹ፦ ሱለይማነል ጀመል ሀዚም የተባሉ ሰው ኢብኑ አባስ አወሩት ብለው እንደገለጹት “እነዚያ እኛ ነሳራዎች (ክርስቲያን) ነን ያሉት ወደ ሙዕሚኖች (ሙስሊሞች) የቀረቡና የተወደዱ ሆነው በርግጥ ታገኛቸዋለህ” (ቁርዓን ማኢዳ፡82) የሚለው የአላህ ንግግር ለሐበሾች እንደሆነ መስክረዋል።
=> የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ.) ስደተኞችን ማስጠለላችን፦ የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ.) የራሳቸው የመካ ህዝቦች ባሰቃዩአቸው ጊዜ መጠጊያ ያልነበራቸው ሰሀቦችን፥ “ወደ ሐበሻ ሂዱ፣ እዛም እርሱ ዘንድ ማንም የማይበድል የሆነ መንግስት ታገኛላችሁ። ፈረጃ እስኪገኝ ድረስም እዛ ቆዩ” በማለት ላኳቸው።
የስደተኛ ቡድኑ 11 ወንዶች እና 4 ሴቶችን ይዞ የነበረ ሲሆን ከእነሱም ዑስማን ኢብኑ አፋን (ነብዩ መሐመድ ከሞቱ በኋላ ሶስተኛው የሙስሊሙ ዓለም መሪ) እና ባለቤታቸው የሆነችውና የነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ.) ልጅ ሩቂያ ይገኙበት ነበር።

እንደዚህም ዙቤይር ኢብኑ አል-አዋም፣ አብደላህ ኢብኑ መስዑድ፣ አብዱራህማን ኢብኑ አውፍ፣ አቡ ሁዘይፋ ኢብኑ ኡትባህ እና ባለቤታቸው ሳህለት ቢንቱ ሱሄይል ኢብኑ ዐምር፣ ሙስዓብ ኢብኑ ዑሜይር፣ አቡ ሰለማ ኢብኑ አብዱልአስወድ እና ባለቤታቸው ዑሙ ሰለማህ ቢንቱ ዑመያህ፣ ዑስማን ኢብኑ መዝዑን፣ አሚር ኢብኑ ረቢዓ እና ባለቤታቸው ለይላ ቢንቱ አቢ ሀሰማህ፣ ሀጢብ ኢብኑ ዑመይር እና ሱሄይል ኢብኑ በይዷዕ ባህር ተሻግረው ወደ ሐበሻ መጥተዋል።
ይህ የመጀመሪያው ስደት ተብሎ የሚታወቅ ሲሆን የመጡበት ጊዜም በረጀብ ወር፣ ነብዩ መሐመድ በተላኩ በ5ኛ ዓመት ነው። ቀጥሎም በጃዕፈር ኢብኑ አቡጣሊብ ከ82 በላይ (82 ማለት ሴቶች ሳይቆጠሩ የወንዶች ቁጥር ብቻ ነው) ሙስሊም ስደተኞች ወደ ሐበሻ ዘልቀዋል።
=> የተሻለ ፍትህ እንዳለን በነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ.) መመስከሩ፦ የበድር ጦርነት በተከሰተና ቁረይሾች በተሸነፉ ጊዜ በቀላቸውን ወደ ሐበሻ በተሰደዱት ላይ ሊወጡ አሰቡ። ሁለት ሰዎችም ስጦታ አስይዘው ወደ ንጉስ ነጃሺ ላኩ።
ነጃሺም ሰሃቦችን ከቁረይሾች አስጥሎ “ሂዱ! በምድሬ ላይ ተረጋግታችሁ ኑሩ” በማለት በሰላም እንዲኖሩ ፈቀደላቸው። ስደተኛ ሙስሊሞችን/ሰሃቦችን ለመበቀል የመጡት የቁረይሽ ሰዎች የከሰሩ ሆነው ወደ ሀገራቸው ተመለሱ። ሙስሊሞቹ ደግሞ በነጃሺና በጥሩ ሀገሩ፣ በጥሩ ጉርብትና ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ.) ወደ መዲና እስከተሰደዱበትና ጠላቶቻቸውን እስኪያንበረክኩ ድረስ በሰላም ቆዩ።
አላህ ሐበሻን አስመልክቶ በቁርዓን ሱረቱል ማኢዳ፡82 እንዲህ ብሏል፦ “. . . በውስጣቸው የተለያዩ ቄሶችና መነኮሳት ያሉ ሲሆን እነርሱም የማይኮሩና ሀቅ በመጣ ጊዜ የሚቀበሉ በመሆናቸው ነው”
=> ነብዩ መሐመድን (ሰ.ዐ.ወ.) ከዑሙ ሀቢባ ጋር ያጋባንና መህሩንም የከፈልን በመሆናችን፦ በ6ኛ ዓመተ ሂጅራ ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ.) ወደ ነጃሺ ደብዳቤ ላኩ። በደብዳቤው ውስጥ ዑሙ ሀቢባ ቢንት አቡ ሱፍያን የተባለች ሴት ከባሏ ጋር ወደ ሐበሻ ተሰዳ ሳለ ባሏ በስደት ላይ በመሞቱ ነብዩ ሊያገቧት እንደፈለጉ የሚገልጸው መልዕክት ይገኝበታል።
ነጃሺም አብርሃ የተባለች ተላላኪያቸውን ወደ ዑሙ ሀቢባ በመላክ የነብዩን (ሰ.ዐ.ወ.) መልዕክት አበሰሩላት። መህርዋም (ሴት ልጅ ስታገባ ከባል የሚሰጥ) 400 ዲናር ሲሆን በነብዩ (ሰ.ዐ.ወ.) ወገን ሆኖ ለኒካሁ ስኬታማነት ትልቁን ሚና የተጫወቱት የሀበሻው ንጉስ ነጃሺ ነበሩ።
=> ንጉሳችን አህመድ ነጃሺ እስልምናን መቀበላቸው፦ ከቆይታ በኋላ ነጃሺ በአላህ ያመኑ መሆናቸውን ገለጹ። ይህንንም “ታማኝና አሳማኝ መልዕክተኛው መሆንህን እመሰክራለሁ” ሲሉ ለነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ.) በላኩት መልዕክት ይፋ አድርገዋል። ነጃሺ መልዕክቱን የላኩት በልጃቸው አዝሀን እና በ60 ባልደረቦቹ አማካኝነት ነው። በመልዕክቱ ውስጥ “. . . ልጄንም አዝሀን ልኬአለሁ። ከፈለግክም እራሴ መምጣት እችላለሁ። የአላህ ሰላም ባንተ ላይ ይሁን . . .” የሚል ይገኝበታል።
=> የነብዩ ቤተሰቦችና ታላላቅ ሰሃባዎች በሀገራችን መኖራቸው፦ የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ.) ልጅ ሩቂያ፣ በጣም የሚወዷቸውና የቅርብ አማካሪያቸው የሆኑት እንዲሆም ለእርሳቸው ያላቸው ከበሬታ የላቀና የሁለት ልጆቻቸው ባለቤት ዑስማን፣ የአላህ ካዝና በእርሱ እጅ ያለ የሚመስለው ሀብታሙ አብዱራህማን፣ ነብዩን (ሰ.ዐ.ወ.) በመልክ የሚመሳሰሉትና የአጎታቸው ልጅ የሆኑት ጃዕፈር፣ የዑለማዎች ኮከብ ተብለው የሚታወቁት ታላቁ አብደላህ ኢብኑ መስዑድ . . . ይህቺን ሀገር መርገጣቸው እንዲሁም ከእነርሱ ክብር ያልተናነሱ ታላላቅ ሰሃባዎች በሐበሻ ምድር በሞት መቅረታቸውና ከቁርዓኑ አያ (አንቀጽ) ጋር ተደማምሮ ከእነርሱ የተያያዘ የነብዩ ሀዲሶች መኖራቸው፤ ነጃሺም የነብዩን እጮኛ ማክበራቸውና መህሩንም በራሳቸው መክፈላቸው፤ የነጃሺ ባለቤቶች የነብዩን እጮኛ በተለያዩ ስጦታዎች ማንበሽበሻቸው . . . ከሌሎች ሀገሮች በተለየ የሐበሻ ታላቅነትና ክብር የሚገለጽባቸው ነጥቦች ናቸው።
=> የቢላል አል-ሐበሻ ወገን መሆናችን፦ እስልምናን በመቀበሉ ምክንያት ከጠላቶች ቅጣትን ከመቀበሉ ባሻገር በቅጣቱ ሰዓት እንኳ ባሳየው ታላቅ ጽናት ከሚያወጣቸው ቃላቶች የተነሳ “ወደ አላህ ተጣሪ” በሚል ከአላህ ሙግስናን አግኝቷል። “ያ እርሱ ወደ አላህ ከሚጣራው የበለጠ ድምጹ ያማረ ማን ነው?”
=> የሐበሻ ምድርና ሕዝቦቿ በሚዕራጅ መታየታቸውና አንድ የኑር ብርሃን በሐበሻ ላይ ማረፉ፦
ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ.) ሚዕራጅ በወጡ ጊዜ በሐበሻ ምድር ብርሃናቸው እንደ ክዋክብት የሆኑ ሰዎች ተመለከቱ። ለጅብሪልም “እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው?” ብለው ጠየቁት። “እነዚህማ ከዑመትህ ውስጥ የሆኑ ሐበሾች ናቸው!” ብሎ መለሰላቸው። ነብዩም “ጌታዬ ሆይ! እርዳቸው!” ብለው ዱዓ አደረጉ።

የመረጃ ምንጭ፦ “ጥሮነ - የኢትዮጵያ ቀደምትና ታላላቅ ዑለማዎች ታሪክ”
ጽሁፍ (አረብኛ)፦ ሼህ ዑመር ሼህ በሽር (ከ1288-1351 ዓመተ ሂጅራ ወይም ከ1860-1923 ዓ.ም)
ትርጉም (ወደ አማርኛ)፦ ሼህ አብደላህ መሐመድ አሊ
የመጽሃፉ አሳታሚ፦ አብዱልፈታህ አብደላህ

ማሳሰቢያ፦ ጽሁፉ ከመጽሃፉ የተወሰደው ሙሉ በሙሉ ሳይሆን ለንባብ እንዲመች በማሰብ በተወሰነ መልኩ እንዲያጥር ተደርጎ ነው።