በአብዱረዛቅ መሐመድ
ዑመር ፋርዳ ተወልዶ ያደገው በአሁኑ አጠራር በጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ ዮሸግ በሚባል አካባቢ
ነው። ዑመር ፋርዳ ጀግና፣ ነገር አዋቂ፣ ደፋር፣ እውነት ፈራጅ፣ እልኸኛ፣ ልበ ሙሉ፣ ቀጠሮ አክባሪ፣ ታማኝና ጠንካራ ገበሬ እንደነበር
ይገለጻል።
ዑመር ፋርዳ በሰባት ቤት ጉራጌ ታሪክ
በመጀመሪያ ደረጃ ከሚታወቁ የጦር ጀግኖች መካከል አንዱ ነበር “ጦርና ዑመር ፋርዳ ተለያዩ ማለት ልክ እንደተሰለበ ወንድ ልጅ ነው” ብሎ ያምን ነበር፡፡
በአንድ ወቅት ዑመር ፋርዳ አጼ ሚኒሊክ ቤተ-መንግስት ለመግባት ጦሩን በትከሻው ይዞ ይመጣል፡፡ ይሁን እንጂ የቤተ-መንግስት ጠባቂዎች ጦሩን ካላስቀመጠ መግባት እንደማይችል ይነግሩታል። እሱም ለጥበቃዎቹ “ለወንድ ልጅ ‘ጦርህን አስረክበኝ’ ብሎ ማለት ቀረብ በልና ልስለብህ ከማለት ቢበልጥ እንጂ የሚተናነስ አይደለም” ሲል ይመልስላቸዋል። በዚህን ጊዜ ጠባቂዎቹ “እንግዲያስ አንተ መግባት አትችልም” አሉት፡፡
በዚህም የተነሳ ከቤተ-መንግስት ጥበቆች
ጋር አለመግባባት ይፈጠራል፤ ጠባቂዎቹም ሁኔታውን ስላስፈራቸው አረጋግተውት ወደ አጼ ምኒሊክ ሄደው ሁኔታውን በመንገር እንዲገባ ተፈቀደለት፡፡ ከገባም በኋላ አጼ ምኒሊክ፥ ዑመር ፋርዳ ጦሩን ለማስቀመጥ ፈቃደኛ ያልሆነበትን ምክንያት ሲጠይቁት ለጥበቃዎቹ የነገራቸውን ደገመላቸው፡፡ ከዚያን ቀን ጀምሮ ዑመር ፋርዳ ቤተ-መንግስት ሲገባ ጦሩን ይዞ እንዲገባ አጼ ምኒሊክ ፈቀዱለት፡፡
በሰባት ቤት ጉራጌ ዑመር ፋርዳን በጦር ጀግንነት የሚወዳደር ሰው ቢኖር የእነሞሩ ላማዳ ነበር፡፡ እነዚህ ሁለቱ የጦር ጀግኖች በድንበር ግጭት እነሞር ውስጥ “የጓረቤ ድብር” በተባለ ቦታ ላይ ሲዋጉ ሁለቱም ቆስለው ወድቀው እንኳን በወደቁበት ጦራቸውን በእግራቸው እየገፉ መዋጋታቸው ይነገራል፡፡
ዑመር ፋርዳ ከሐሰን አንጃሞ ጋር በመሆንም በራስ ጐበና ይመራ ከነበረው የአጼ ሚኒሊክ ጦር ጋር ተዋግቷል፡፡ በተጨማሪም በወቅቱ ከነበሩ ጦረኞች ጋር ተዋግቶ ድልን በመጎናጸፍ ጀግነቱን አሳይቷል፡፡
ዑመር ፋርዳ በሰባት ቤት ጉራጌ አካባቢ በቀጠሮ አክባሪነት የሚስተካከለው ሰው እንዳልነበረ ይነገርለታል። አባቶችና የታሪክ ጸሃፊዎች “ዑመር ፋርዳ በቀጠሮ አክባሪነቱ ለጉራጌ ህዝብ ታሪክ ሰርቶ አልፏል” ይላሉ፡፡
በአንድ ወቅት እንደተለመደው ጦሩን ይዞ በህዝብ መካከል ቆሞ “ይህ ጦር ማን ይወጋበት?” ብሎ ለህዝቡ ይጠይቃል፤ ህዝቡም እገሌ ብሎ ለመፍረድ ሲከብደው እሱ ለጥያቄው መልስ ሰጠ። “በዚህ ጦር መወጋት ያለበት ወይም የሚገባው በቀጠሮ የሚቀር ሰው ነው” በማለት ታሪካዊ አባባል ጥሎ አልፏል፡፡ እስከዛሬም ይህን አባባል የጉራጌ ህዝብ ዘንድ ቀጠሮ እንዲከበር ይጠቀምበታል፡፡
ዑመር ፋርዳ ለቀጠሮ አክባሪነቱ ተጨማሪ ማሳያ የሚሆነው፣ ከአንድ የጦር ተፎካካሪው ጋር ለመዋጋት ቀጠሮ በያዙበት እለት ለአቅመ አዳም ደርሳ የነበረች ልጁ ሞታበት ሰዉ ወደ መቃብር ስነ-ስርዓት ቦታ ሲሄድ እሱ “ፈረሴን ጫኑልኝ! ለውጊያ ቀጠሮ ይዣለሁ!” በማለት ልጁን ሳይቀብር ለውጊያ እንደዘመተ ይነገራል።
ዑመር ፋርዳ አዋቂና እውነት ፈራጅ ከሚባሉ ታላላቅ ሰዎች የሚመደብ ነበር፡፡ ዑመር ፋርዳ አዋቂነቱና እውነት ፈራጅነቱን ያስመሰከረው በአንድ ወቅት የአንድ የመኳንንት ወገን የነበረ ከአንድ ተራ ሰው ይጣላና ጉዳዩ በወቅቱ የፍርድ ውሳኔ ወደ ሚሰጡት ከፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ ችሎት በተጋበዘበት ወቅት ነበር፡፡ በዘውዳዊ አገዛዝ ስርዓት ወቅት የአንድ መኳንንት ወይም መሳፍንት ዘር በተራ ሰው መደፈር እንደ ከፍተኛ ወንጀል ተደርጐ ይታይ ነበር፡፡ ችሎቱም “ነገ በእኔ ነውና” በሚል አስተሳሰብ ሁሉም በአንድ ድምፅ ይህ ድርጊት ወደ ሞት የሚያስገባ ነውና በተራ ተብዬው ሰው ላይ የሞት ቅጣት ይወስናሉ፡፡
በችሎት የተጋበዘው ዑመር ፋርዳ በሃሳቡ ሳይስማማ በመቅረቱ የበኩሉን ፍርድ እንዲሰጥ እድል ተሰጠው፡፡ ችሎቱ ከሁሉም መኳንንት ውሳኔ የተለየ ይሰጣል ብሎ ባልገመተበት ሁኔታ ዑመር ፋርዳ ውሳኔ ለመስጠት በጥያቄ ነበር የጀመረው፡፡ “ለመሆኑ ይህ ተከሳሽ ሰውን ገደለ ወይ?” ብሎ ሲጠይቅ “አልገደለም፣ ሆኖም አንድ የመኳንንት ወገን ከመደፈሩ በላይ አካሉን አጐደለ ብለው ነው” ሲሉት “ታድያ ያልገደለ መግደል አግባብ አይደለም፤ ሌላ ተመጣጣኝ ፍርድ ይሰጠው” ብሎ ፈረደ፡፡ በዚህ ጊዜ ፊታውራሪ ኃብተጊዮርጊስ የዑመር ፋርዳ አጠያየቅና የፍርድ አሰጣጥ አድንቀው የተከሳሹ ፍርድ ከሞት ቅጣት ወደ ግርፋት ተቀይሮ ውሳኔ ከሰጡት በኋላ ለፋርዳም “እዚህ እስካለህ ድረስ ከችሎት እንዳትለይ” ብለው ተማፀኑት ይባላል፡፡
ዑመር ፋርዳ በልበ ሙሉነቱ እጅግ የሚደነቅ ሰው ነበር፡፡ የአጼ ምኒሊክ መንግስት በራስ ጐበና ዳጨ አማካኝነት ሰባት ቤት ጉራጌን በስልጣኑ ስር ለማድረግ ከተቆጣጠረ በኋላ ኡመር ፋርዳ ወደ አንኮበር ተወስዶ ታስሮ ነበር፡፡ ከተወሰነ እስራት በኋላ ፈተውት ፊታውራሪ ኃብተጊዮርጊስ ዘንድ እንዲቀርብ አድርገው መታረሙንና ለአጼ ምኒሊክ መንግስት ያለውን አክብሮት ለማረጋገጥ “ፋርዳ ምንድን ነው የምትፈራው?” ብለው ሲጠይቁት “እኔ የምፈራው ፈጣሪን እና ረሃብን ብቻ ነው” አለ ይባላል፡፡
ዑመር ፋርዳ ከሚታወቅባቸው ነገሮች አንዱ ታማኝነቱ ነው፡፡ ለሚስቱና ለትዳሩ እጅግ ታማኝ ሰው ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት በቤተ-ጉራጌ ዘንድ እንደሱ ያለ ታማኝ ብልህና አዋቂ ልጅ እንዲያገኝ ምኞቱ የላቀ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ አንዲት የቸሃ ዋቅ /የባህላዊ አምልኮ/ የበላይ ተጠሪ የነበረች እንደ በሮሬት የተባለች ሴት ከፋርዳ ልጅ ለመውለድ ፈልጋ ወጥመዷን መዘርጋት ትጀምራለች፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አመሻሽ ላይ እቤቷ ድረስ በመጋበዝ በሬ ታርድለታለች፤ የሚፈልገውን ምግብ እንዲመገብና መጠጥም እንዲጠጣ አደረገችው፤ በኋላ ወደ መኝታ ሲገባ እሷ አጠገቡ ጋደም ብላ ወገቡን በለጋ ቅቤ በማሻሸት ዝሙት እንዲፈፅም ገፋፋችው፤ እሱም ይህን በተረዳ ጊዜ በከፍተኛ ቁጣና ስደብ ብድግ ብሎ በመነሳት በሌሊት ተነስቶ ፈረሱን ጭኖ ጦሩን በትከሻው ተሽክሞ ወደ ቤቱ ነበር የሄደው፡፡ (በዚያው እለት ከውድ ባለቤቱ ጋር ተገናኝቶ ባሻ ናስር የተባለው ታዋቂ ልጅ ተፀንሶ እንደተወለደ ይነገራል፡፡)
ሼህ ዑመር (የወለኔ ሼህ)
(1860-1923 ዓ.ም) በመጽሃፋቸው እንደገለጹት ዑመር ፋርዳ የሐሰን ኢንጃሞ ኸሊፋነት በሰፈነበት ዘመን የሰለሙ ናቸው።
እስልምናን ከተቀበሉ በኋላ ለኢስላም የቀኝ እጅ ነበሩ፤ እስልምና ከፍ አደረጋቸው፤ ልዕልናም አጎናጸፋቸው። ዑመር ፋርዳ በልበ ሙሉነታቸው፣
በጀግንነታቸውና በጉልበታቸው እጅግ የተደነቁ፣ የተፈሩና የታፈሩ ሰው ነበሩ። ዑመር ፋርዳ እውነትን ለማጉላትና ሐሰትን (ባጢልን)
ለመዋጋት ምንጊዜም ዝግጁ ነበሩ።
፡
፡
ስለ ዑመር ፋርዳ በርካታ የሚነገሩ ታሪኮች
ቢኖሩም ተዓማኒ የታሪክ ማጣቀሻዎች ሲገኙ (ሳገኝ) በዝርዝር እመለስባቸዋለሁ!
፡
የመረጃ ምንጮች፦
“ጉራጌ ማነው?” የተሰኘ መጽሃፍ
“የኢትዮጵያ ቀደምትና ታላላቅ
ዑለማዎች ታሪክ” (በሼህ ዑመር ሼህ በሽር)
አቶ ስንታየሁ ተሰማ
የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮምዩኒኬሽን
ጉዳዮች ጽህፈት ቤት