Saturday 2 April 2022

ኢትዮጵያዊው ቢላል ኢብኑ ረባህ




በአብዱረዛቅ መሐመድ

በእስልምና ታሪክ የመጀመሪያው አዛን አድራጊ (ሙዓዚን) ቢላል ኢብን ረባህ (رَبَاح ٱبْن بِلَال) የተወለደው ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ከተወለዱበት መካ (ቅዱስ ከተማ) ውስጥ ሲሆን ታማኝና በነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ልብ ዉስጥ ልዩ ቦታ የነበረው ሰሐባ ነበር። ቢላል እስልምናን የተቀበለዉ በወጣትነት እድሜው ነበር።

በጣም ውብና ልዩ በሆነው ድምጹ የሚታወቀው ቢላል ከእስልምና በፊት በነበረው ህይወቱ “ባሪያ” ነበር። ወላጆቹም ከሐበሻ ምድር (ኢትዮጵያ) ወደ መካ የሄዱ ባርያዎች ስለመሆናቸው በታሪክ ተጽፎ ይገኛል። የቢላል አባት ረባህ ሲሆን እናቱ ደግሞ ሐማም ትባላለች። እንዲሁም ባለቤት ደግሞ ሂንድ ትባላለች።

ቢላል አል ሐበሽይ፣ ቢላል ኢብን ሪያህ እና ቢላል ኢብን ረባህ ይጠራባቸው ከነበሩ ሶስት ስሞች ናቸው።

ቢላል ከእስልምና በፊት በነበረው ህይወቱ የበኒ ጁመሃ ጎሳ አባል የነበረው የኡመያ ኢብን ኸለፍ ባሪያ ነበር። አንድ ቀን ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በነብይነት የመላካቸው ዜና የመካ ህዝብ ሲቀባበለው ከቢላል ጆሮ ደረሰ። የቢላል አሳዳሪ ከእንግዶቹ ጋር ስለ ነብዩ መላክ እና ጣዖታቸውን እንደሚቃወም በንዴት እየተብሰለሰለ እና ሴራ እያውጠነጠነ ሲናገር ቢላል ሰማ፤ ቢላል ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ስለተነሱበት ዓላማና ስለሚያስተምሩት ትምህርት ግንዛቤ ሊያገኝ ቻለ።

አዲስ የመጣው ሐይማኖት ለአካባቢው ማህበረሰብ እንግዳ ነገር እንደሆነና እና ስር-ነቀል ለውጥ ለማምጣት ያለመ ስለመሆኑ፤ ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ምንም እንኳን “ነብይ ነኝ” ብለው በመናገራቸው ተቃውሞ የገጠማቸው ቢሆንም ታማኝ፣ እውነተኛ እና በስነ ምግባር የታነጹ ስለመሆናቸው ቢላል ከነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ጠላቶች አንደበት አደመጠ። “መሐመድ አንድም ቀን ዋሽቶ አያውቅም፤ ጠንቋይም ሆነ እብድ አይደለም:... ሆኖም ዛሬ እኛ እርሱን በነዚህ ነገሮች መጥላት ይኖርብናል። ወደ እርሱ የሚጎርፉትን ሰዎች መግታት የምንችለው በዚህ መንገድ ነው።” በማለት ሲዶልቱ ቢላል ታዝቧል።

ከእለታት በአንዱ ቢላል የእምነት ምርጫውን ይፋ ማድረግ እንዳለበት ወሰነ፤ ወደነብዩ መሐመድ በመሄድ እስልምና ለመቀበል መወሰኑን ይፋ አደረገ። በዚህን ጊዜ የቢላል መስለም በመካ ምድር ተሰራጨ። የበኒ ጁመሃ መሪዎች ይህን ዜና ሲሰሙ ክፉኛ ተቆጡ፤ በተለይም ኡመያ ኢብን ኸለፍ የተባለው የቢላል አሳዳሪ የ”ባሪያ”ው መስለም እንደ ታላቅ ነውር እና ንቀት ቆጠረው። ኡመያ እንዲህም አለ፥ “ይህ ኮብላይ ባሪያ በመስለሙ ጸሀይ ተመልሳ የምትጠልቅ አይመስለኝም”

ኡመያና የበኒ ጁመሃ ጎሳ መሪዎች ለቢላል ከእስልምና እንዲወጣ እና በወቅቱ ይመለኩ በነበሩት ”ላት እና ኡዛ” በሚባሉ ጣዖታት እንዲያምን ደጋግመው ጠየቁት። ቢላል ግን እስልምናውን አጥብቆ እንደሚይዝ ገለጸለት። ሊያምንላቸው ስላልቻለ በመካ በረሃ በጸሀይ በተቃጠለ አሽዋማ መሬት ላይ አስሮ አስተኝተውና ሆዱ ላይ ትልቅ ድንጋይ አስቀምጠው በግርፋት ሲቀጡት ቢላል ግን ከስጋዊ ህመም መንፈሳዊ የበላይነትን በመምረጡ ለጠላቶቹ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም። ይልቁንም በተደጋጋሚ “አሐድ! አሐድ” አሐድ! ... “ በማለት የአምላክን አንድነት ያውጅ ነበር።

ቢላል በርካታ ኢሰብዓዊ ድርጊት ተፈጽሞበታል። የበኒ ጁመሃ ጎሳ መሪዎች አንድን ባሪያ አሳምነው ወደ ቀድሞ እምነቱ ሊመልሱት ባለመቻላቸው ቁጭት እና ሀፍረት ተሰማቸው፤ ክብራቸውን ለመጠበቅ ሲሉ ቢላል ቢያንስ ስለ አማልክቶቻቸው ጥቂት በጎ ነገር እንዲናገር ቢጠይቁትም አሻፈረኝ አለ። ህይወቱን ከስቃይ ምናልባትም ከሞት ለማዳን ከልቡ ባይሆንም እንኳ ቢያንስ ስለ አማልክቶቻቸው ጥሩ መናገር በቂው ነበር። ቢላል ግን ለኢስላም ብቻ ሳይሆን ለመላው የሰው ዘር የሚያኮራ ጠንካራ አቋም ወሰደ።

“እኛ የምንለውን ደግመህ በል” በማለት ይገርፉታል። እሱም “እናንተ የምትሉትን ለመናገር ምላሴ አይችልም” ይላቸዋል። በዚህን ጊዜ ነበር አቡበክር ሲዲቅ (ረ.ዐ.) የመጡት። አቡበክር መጡና ቢላልን ከኡመያ ለመግዛት ተስማሙ። አቡበክርም ቢላልን ለራሳቸው ባሪያ ሊያደርጓቸው አልፈለጉም፤ ይልቅ ከስቃዩ ገላግለው ነጻነቱን አወጁለት።

ነጻነቱን ካገኘ በኋላ ወደ ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) በመሄድ ሙሉ ጊዜውን ለእስልምና ሰጠ። ነብዩ መሐመድም ቢላልን ለአዛን አድራጊነት (ሙዓዚንነት) መረጡት። በተጨማሪም የመዲና የግምጃ ቤት (በይተል ማል) ኃላፊ አድርገው ሾሙት። ቢላል በዚህ የግምጃ ቤት ኃላፊነት እያለ ባላቸው ለሞተባቸው ሴቶች፣ ለወላጅ አልባ ህጻናት፣ ለመንገደኞች እንዲሁም እራሳቸውን መርዳት ለማይችሉ ሌሎች ሰዎችም የገንዘብና ቁሳቁስ አከፋፍሏል።

ሙሐመድ አብድልረዑፍ የተባለ ጸሐፊ ስለ ቢላል በጻፈው መጽሃፉ፥ “ቢላል ውብና ማራኪ የሰውነት ቅርጽ፣ ጥቁር ቡናማ የፊት ቀለም፣ አብረቅራቂ አይኖች፤ የተስተካከለ አፍንጫና የጠራ ቆዳ ነበረው። በተጨማሪም ወፍራም፣ ሙዚቃዊ ቃና ያለውና አስገምጋሚ ድምጽ የታደለ ሰው ነበር። እንዲሁም በሁለቱም ጉንጮቹ በኩል ሳሳ ያለ ጺም ነበረው። ቢላል ትልቅ እውቀት የተቸረው፣ ለራሱ ክብር የሚሰጥና በራሱ የሚተማመን ሰው ነበር” ይላል።

ዊልያም ሙዒር የተባለ ጸሃፊ በበኩሉ፥ “ቢላል ረጅምና ጥቁር ሲሆን አፍሪካዊ የፊት ቅርጽና ጥቅጥቅ ብሎ የሚበቅል ጸጉር ነበረው።” ጸሐፊው አክሎም የቁረይሽ ጎሳ አባላት ቢላልን ‘የጥቁር ሴት ልጅ’ (“ኢብን ሰውዳ/Ibn Sawda”) እያሉ ይሰድቡት ነበር” ብሏል።

ቢላል ኢብኑ ረባህ ጓደኞቹ ሲያሞጋግሱት አንገቱን ይደፋ እንደነበርና አይኖቹን በትዝታ ገርበብ አድርጎ “ትናንት ባሪያ የነበርኩ ሀበሻ ነኝ” ይል ነበር። እነሱ ግን “የእኛ ልዑል” ብለው ይጠሩት እንደነበር ታሪክ ጽፏል።

ቢላል የተወለደው በፈረንጆቹ መጋቢት 05፣ 580 ሲሆን ህይወቱ ያለፈው ግን ከ638-40 ባለው ጊዜ ውስጥ (ከዚህ ጋር በተያያዘ ያሉ መረጃዎች የተለያዩ ናቸው) እንደሆነ ይነገራል።


ምንጮች፦

Study papers and documents titled: 

Bilal ibn Rabah
The Life of Muhammad
Lessons from the Lives of the Sahaba
Bilal ibn Rabah: The symbol of human equality

Friday 1 May 2020

ዑመር ፋርዳ

በአብዱረዛቅ መሐመድ

ዑመር ፋርዳ ተወልዶ ያደገው በአሁኑ አጠራር በጉራጌ ዞን ቸሃ ወረዳ ዮሸግ በሚባል አካባቢ ነው። ዑመር ፋርዳ ጀግና፣ ነገር አዋቂ፣ ደፋር፣ እውነት ፈራጅ፣ እልኸኛ፣ ልበ ሙሉ፣ ቀጠሮ አክባሪ፣ ታማኝና ጠንካራ ገበሬ እንደነበር ይገለጻል።
ዑመር ፋርዳ በሰባት ቤት ጉራጌ ታሪክ በመጀመሪያ ደረጃ ከሚታወቁ የጦር ጀግኖች መካከል አንዱ ነበር “ጦርና ዑመር ፋርዳ ተለያዩ ማለት ልክ እንደተሰለበ ወንድ ልጅ ነው” ብሎ ያምን ነበር፡፡
በአንድ ወቅት ዑመር ፋርዳ አጼ ሚኒሊክ ቤተ-መንግስት ለመግባት ጦሩን በትከሻው ይዞ ይመጣል፡፡ ይሁን እንጂ የቤተ-መንግስት ጠባቂዎች ጦሩን ካላስቀመጠ መግባት እንደማይችል ይነግሩታል። እሱም ለጥበቃዎቹ  ለወንድ ልጅጦርህን አስረክበኝ’ ብሎ ማለት ቀረብ በልና ልስለብህ ከማለት ቢበልጥ እንጂ የሚተናነስ አይደለም”ል ይመልስላቸዋል። በዚህን ጊዜ ጠባቂዎቹእንግዲያስ አንተ መግባት አትችልም” አሉት፡፡
በዚህም የተነሳ ከቤተ-መንግስት ጥበቆች ጋር አለመግባባት ይፈጠራል፤ ጠባቂዎቹም ሁኔታውን ስላስፈራቸው አረጋግተውት ወደ አጼ ምኒሊክ ሄደው ሁኔታውን በመንገር እንዲገባ ተፈቀደለት፡፡ ከገባም በኋላ አጼ ምኒሊክ፥ ዑመር ፋርዳ ጦሩን ለማስቀመጥ ፈቃደኛ ያልሆነበትን ምክንያት ሲጠይቁት ለጥበቃዎቹ የነገራቸውን ደገመላቸው፡፡ ከዚያን ቀን ጀምሮ ዑመር ፋርዳ ቤተ-መንግስት ሲገባ ጦሩን ይዞ እንዲገባ አጼ ምኒሊክ ፈቀዱለት፡፡
በሰባት ቤት ጉራጌ ዑመር ፋርዳን በጦር ጀግንነት የሚወዳደር ሰው ቢኖር የእነሞሩ ላማዳ ነበር፡፡ እነዚህ ሁለቱ የጦር ጀግኖች በድንበር ግጭት እነሞር ውስጥየጓረቤ ድብር” በተባለ ቦታ ላይ ሲዋጉ ሁለቱም ቆስለው ወድቀው እንኳን በወደቁበት ጦራቸውን በእግራቸው እየገፉ መዋጋታቸው ይነገራል፡፡
ዑመር ፋርዳ ከሐሰን አንጃሞ ጋር በመሆንም በራስ ጐበና ይመራ ከነበረው የአጼ ሚኒሊክ ጦር ጋር ተዋግቷል፡፡ በተጨማሪም በወቅቱ ከነበሩ ጦረኞች ጋር ተዋግቶ ድልን በመጎናጸፍ ጀግነቱን አሳይቷል፡፡
ዑመር ፋርዳ በሰባት ቤት ጉራጌ አካባቢ በቀጠሮ አክባሪነት የሚስተካከለው ሰው እንዳልነበረ ይነገርለታል። አባቶችና የታሪክ ጸሃፊዎች “ዑመር ፋርዳ በቀጠሮ አክባሪነቱ ለጉራጌ ህዝብ ታሪክ ሰርቶ አልፏል” ይላሉ፡፡
በአንድ ወቅት እንደተለመደው ጦሩን ይዞ በህዝብ መካከል ቆሞይህ ጦር ማን ይወጋበት?” ብሎ ለህዝቡ ይጠይቃል፤ ህዝቡም እገሌ ብሎ ለመፍረድ ሲከብደው እሱ ለጥያቄው መልስ ሰጠ። “በዚህ ጦር መወጋት ያለበት ወይም የሚገባው በቀጠሮ የሚቀር ሰው ነው” በማለት ታሪካዊ አባባል ጥሎ አልፏል፡፡ እስከዛሬም ይህን አባባል የጉራጌ ህዝብ ዘንድ ቀጠሮ እንዲከበር ይጠቀምበታል፡፡
ዑመር ፋርዳ ለቀጠሮ አክባሪነቱ ተጨማሪ ማሳያ የሚሆነውከአንድ የጦር ተፎካካሪው ጋር ለመዋጋት ቀጠሮ በያዙበት እለት ለአቅመ አዳም ደርሳ የነበረች ልጁ ሞታበት ሰዉ ወደ መቃብር ስነ-ስርዓት ቦታ ሲሄድ እሱፈረሴን ጫኑልኝ! ለውጊያ ቀጠሮ ይዣለሁ!” በማለት ልጁን ሳይቀብር ለውጊያ እንደዘመተ ይነገራል።
ዑመር ፋርዳ አዋቂና እውነት ፈራጅ ከሚባሉ ታላላቅ ሰዎች የሚመደብ ነበር፡፡ ዑመር ፋርዳ አዋቂነቱና እውነት ፈራጅነቱን ያስመሰከረው በአንድ ወቅት የአንድ የመኳንንት ወገን የነበረ ከአንድ ተራ ሰው ይጣላና ጉዳዩ በወቅቱ የፍርድ ውሳኔ ወደ ሚሰጡት ከፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ ችሎት በተጋበዘበት ወቅት ነበር፡፡ በዘውዳዊ አገዛዝ ስርዓት ወቅት የአንድ መኳንንት ወይም መሳፍንት ዘር በተራ ሰው መደፈር እንደ ከፍተኛ ወንጀል ተደርጐ ይታይ ነበር፡፡ ችሎቱምነገ በእኔ ነውና” በሚል አስተሳሰብ ሁሉም በአንድ ድምፅ ይህ ድርጊት ወደ ሞት የሚያስገባ ነውና በተራ ተብዬው ሰው ላይ የሞት ቅጣት ይወስናሉ፡፡
በችሎት የተጋበዘው ዑመር ፋርዳ በሃሳቡ ሳይስማማ በመቅረቱ የበኩሉን ፍርድ እንዲሰጥ እድል ተሰጠው፡፡ ችሎቱ ከሁሉም መኳንንት ውሳኔ የተለየ ይሰጣል ብሎ ባልገመተበት ሁኔታ ዑመር ፋርዳ ውሳኔ ለመስጠት በጥያቄ ነበር የጀመረው፡፡ለመሆኑ ይህ ተከሳሽ ሰውን ገደለ ወይ?” ብሎ ሲጠይቅአልገደለም፣ ሆኖም አንድ የመኳንንት ወገን ከመደፈሩ በላይ አካሉን አጐደለ ብለው ነው” ሲሉትታድያ ያልገደለ መግደል አግባብ አይደለም ሌላ ተመጣጣኝ ፍርድ ይሰጠው” ብሎ ፈረደ፡፡ በዚህ ጊዜ ፊታውራሪ ኃብተጊዮርጊስ የዑመር ፋርዳ አጠያየቅና የፍርድ አሰጣጥ አድንቀውተከሳሹ ፍርድ ከሞት ቅጣት ወደ ግርፋት ተቀይሮ ውሳኔ ከሰጡት በኋላ ለፋርዳምእዚህ እስካለህ ድረስ ከችሎት እንዳትለይ” ብለው ተማፀኑት ይባላል፡፡
ዑመር ፋርዳ በልበ ሙሉነቱ እጅግ የሚደነቅ ሰው ነበር፡፡ የአጼ ምኒሊክ መንግስት በራስ ጐበና ዳጨ አማካኝነት ሰባት ቤት ጉራጌን በስልጣኑ ስር ለማድረግተቆጣጠረ በኋላ ኡመር ፋርዳ ወደ አንኮበር ተወስዶ ታስሮ ነበር፡፡ ከተወሰነ እስራት በኋላ ፈተውት ፊታውራሪ ኃብተጊዮርጊስ ዘንድ እንዲቀርብ አድርገው መታረሙንና ለአጼ ምኒሊክ መንግስት ያለውን አክብሮት ለማረጋገጥፋርዳ ምንድን ነው የምትፈራው?” ብለውጠይቁትእኔ የምፈራው ፈጣሪን እና ረሃብን ብቻ ነው” አለ ይባላል፡፡
ዑመር ፋርዳ ከሚታወቅባቸው ነገሮች አንዱ ታማኝነቱ ነው፡፡ ለሚስቱና ለትዳሩ እጅግ ታማኝ ሰው ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት በቤተ-ጉራጌ ዘንድ እንደሱ ያለ ታማኝ ብልህና አዋቂ ልጅ እንዲያገኝ ምኞቱ የላቀ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ አንዲት የቸሃ ዋቅ /የባህላዊ አምልኮ/ የበላይ ተጠሪ የነበረች እንደ በሮሬት የተባለች ሴት ከፋርዳ ልጅ ለመውለድ ፈልጋ ወጥመዷን መዘርጋት ትጀምራለች፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አመሻሽ ላይ እቤቷ ድረስ በመጋበዝ በሬ ታርድለታለች፤ የሚፈልገውን ምግብ እንዲመገብና መጠጥም እንዲጠጣ አደረገችው፤ በኋላ ወደ መኝታ ሲገባ እሷ አጠገቡ ጋደም ብላ ወገቡን በለጋ ቅቤ በማሻሸት ዝሙት እንዲፈፅም ገፋፋችው፤ እሱም ይህን በተረዳ ጊዜ በከፍተኛ ቁጣና ስደብ ብድግ ብሎ በመነሳት በሌሊት ተነስቶ ፈረሱን ጭኖ ጦሩን በትከሻው ተሽክሞ ወደ ቤቱ ነበር የሄደው፡፡ (በዚያው እለት ከውድ ባለቤቱ ጋር ተገናኝቶ ባሻ ናስር የተባለው ታዋቂ ልጅ ተፀንሶ እንደተወለደ ይነገራል፡፡)
ሼህ ዑመር (የወለኔ ሼህ) (1860-1923 ዓ.ም) በመጽሃፋቸው እንደገለጹት ዑመር ፋርዳ የሐሰን ኢንጃሞ ሊፋነት በሰፈነበት ዘመን የሰለሙ ናቸው። እስልምናን ከተቀበሉ በኋላ ለኢስላም የቀኝ እጅ ነበሩ፤ እስልምና ከፍ አደረጋቸው፤ ልዕልናም አጎናጸፋቸው። ዑመር ፋርዳ በልበ ሙሉነታቸው፣ በጀግንነታቸውና በጉልበታቸው እጅግ የተደነቁ፣ የተፈሩና የታፈሩ ሰው ነበሩ። ዑመር ፋርዳ እውነትን ለማጉላትና ሐሰትን (ባጢልን) ለመዋጋት ምንጊዜም ዝግጁ ነበሩ።
ስለ ዑመር ፋርዳ በርካታ የሚነገሩ ታሪኮች ቢኖሩም ተዓማኒ የታሪክ ማጣቀሻዎች ሲገኙ (ሳገኝ) በዝርዝር እመለስባቸዋለሁ!
የመረጃ ምንጮች፦
ጉራጌ ማነው?” የተሰኘ መጽሃፍ
“የኢትዮጵያ ቀደምትና ታላላቅ ዑለማዎች ታሪክ” (በሼህ ዑመር ሼህ በሽር)
አቶ ስንታየሁ ተሰማ
የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት